Thursday, February 14, 2013

ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር በመንግስት የደረሰበትን አፈና አጋለጠ



564068_215565508573837_1152286427_n

February 14, 2013



ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ጠቅላላ ጉባዔ እንዳናደርግ ስብሰባ እንዳንሰበስብና ቋሚ አመራሮችን እንዳንመረጥ ተደርገናል ሲሉ የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ፡፡

ማህበሩ እንዳስታወቀው በሰሜን ሆቴል፣ በፓኖራማ ሆቴል፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ማሰልጠኛ ተቋም አዳራሾች ጉባኤ ለማካሄድ በደብዳቤ ጠይቀን ስምምነት ላይ ከደረስን በኋላ የማህበሩን ጠቅላላ ጉባዔ እንዳናደርግ ተደርገናል ሲሉ የተስማሙበትን ማስረጃ አያይዘው አቅርበዋል፡፡

ethiopian-envየማህበሩ አመራሮች ጨምረውም በአባሎቻችን ወጣቶች ላይ የአካል ጥቃት በማድረስና የሀሰት ክስ በመመስረት የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አባላትና የደህንነት አባላት ነን የሚሉ ግለሰቦች እንቅፋት እየፈጠሩብን ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ በተለይም የማህበሩ አመራር አባል የሆነችውን ወጣት ወይንሸት ስለሺን ታህሳስ 30 ቀን 2005 ዓ.ም በማህበሩ ቢሮ አካባቢ ሳለች መርፌ በመውጋትና አፍኖ በመውሰድ ለአንድ ሌሊት በኤሌክትሪክ ሾክድ በማድረግና በብረት በመምታት ካሰቃዩአት በኋላ መንገድ ዳር ጥለዋት ሄደው ጉዳዩ በፖሊስ እየተጣራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ የወጣት ወይንሸት ጉዳት በህክምና ማስረጃ የተረጋገጠ ሲሆን ያሰቃዩበትም ምክንያት የማህበሩ አመቻች ኮሚቴ ዋና ሊቀመንበር የሆነው ወጣት ሀብታሙ አያሌው ከአሸባሪ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ይገናኛል ብለሽ እመኚ በሚል እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር አያይዞም ማህበራችን ነፃ ማህበር ነው፣ ነገር ግን አዳራሾችን ገንዘብ ከፍለን እንኳ እንዳንሰበሰብ በመደረጉና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለተባበሩን ለመጠቀም ተገደናል እንጂ የማንም የፖለቲካ ድርጅትን ወግኖ እንደማይሰራ ገልፀዋል፡፡ በግል መገናኛ ብዙኋን በተለይም ፍትህ ጋዜጣ፣ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣና አዲስ ታይምስ መፅሔት ከህትመት እንዲቋረጡ መደረጉ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 ላይ የተቀመጠውን ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን የሚጋፋ በመሆኑ እንደሚቃወም ገልጧል፡፡

ሌላው ወጣቶች በሀገራቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማህበሩ እየሰራ ቢሆንም የባለራዕይ አባላት ብቻ ተለቅመው የሥራ እድሉ እየተነፈጋቸው ነው፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ኤርፖቶች ድርጅት የጉልበት ስራ የሚሰሩ ወጣቶች ማክቤል በተባለ ኤጀንሲ ተመልምለውና የአሻራ ምርመራ አድርገው ውጤታቸውን ያስገቡ ቢሆንም የማህበሩ አባላት ብቻ ተለይተው የሥራ እድሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የተደረጉ ሲሆን ስራውን ያከናወነው ኤጀንሲም ከማህበሩ ጋር ግንኙነት አለው በሚል እድሉን መነጠቁን አስታውቋል፡፡ ከማክቤል የተነጠቀው እድልም መሊፎ (ማህበር፣ሊግ፣ፎረም) የተባለ ድርጅት በማቋቋም በኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ በኩል ብቻ ምልመላው እንዲካሄድ ተደርጓል፤ ይህም በዜጎች መካከል ልዩነትና አድሎአዊነትን በመፍጠር ህገ-መንግስቱን የጣሰ በመሆኑ ማህበሩ አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጧል፡፡

በመጨረሻም በመጪው ሚያዚያ 2005 ዓ.ም ለሚደረገው ምርጫ የህዝብ ታዛቢ ለመሆን ከ3 ወራት በፊት እንደማንኛውም የሲቪክ ማህበር በደብዳቤ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን መልስ እንዳልተሰጠው፤ ነገር ግን በኢቲቪ ለሲቪክ ማህበራት ምርጫውን እንዲታዘቡ ፍቃድ እንደሰጠ አድርጎ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለፁ የቦዱን ነፃ አለመሆን የሚገልፁ አካላትን ትክክለኛነት የሚያሳይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በመግለጫው ወቅትም በአዲስ አበባ የሚገኙ የ‹‹ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር›› የሁሉም ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ በመስጠት ማህበሩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን መገንባት ዋነኛ አላማው በማድረግ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

No comments:

Post a Comment