Tuesday, February 12, 2013

Patriotic Ethiopians in Sweden and Norway accord human rights activist Tamagn Beyene a hero's welcome!








ESAT Daliy News  - Amsterdam Feb 11 2013



   
 



ESAT Fundraising  on February 10, 2013 Oslo, Norway 

 በስዊድን 136 000 ክሮነር ለኢሳት ተሰበሰበ

*የገንዘቡ መጠን በስዊድን ከክብረወሰን ተመዝግቧል

*ሙስሊሙና ክርስቲያኑ አንድነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳይቷል

Artist and activist Tamagne Beyene in Sweden
Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. February 11, 2013)፦

ቅዳሜ የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም በተካሄደው የኢሳት (የኢትዮጵያ ሳተላይ ቴሌቭዥን) የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 136 ሺህ የስዊድን ክሮነር የተሰበሰበ ሲሆን፤ በዚህ ዝግጅት ላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተሳትፎ ያደረጉበት መሆኑ ታውቋል።

አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በተገኘበት በዚሁ ዝግጅት ላይ ወደ ሦስት መቶ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን፣ ወጣት ኤርትራውያን እንዲሁም ስዊድናውያን ተገኝተዋል። ዝግጅቱ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ይጀምራ የተባለ ቢሆንም፤ ከሁለት ሰዓት በላይ አርፍዶ ተጀምሮ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ተጠናቅቋል። በስዊድን ከተደረጉ ዝግጅቶች ውስጥ ይኸኛው ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ አንድነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያሳየበት መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለመረዳት ችሏል።
በዝግጅቱ ላይ የስዊድን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርላማ አባልና የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ተወካይ የሆኑት ክብርት ካሪና ሄግ እንዲሁም በኢትዮጵያ ታስረው ከነበሩት የስዊድን ጋዜጠኞች አንዱ ማርቲን ሺቤ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

Ethiopian Muslims and Christians in Sweden

ዝግጅቱን በንግግር እንዲከፍቱ የተጋበዙት የክርስትና እና የእስልምና ኃይማኖት አባቶች ነበሩ። እነርሱም ቀሲስ ፍሰኀ ከክርስትናው እና አቶ ሶፊያን ከእስልምና ኃይማኖት ሲሆኑ፣ ሁለቱም አባቶች ጎን ለጎን በመቆም ባደረጉት ንግግር የታዳሚዎችን ቀልብ የሳበ ንግግር አድርገዋል። የኃይማኖት አባቶቹ የኢትዮጵያን ታሪክ ከኃይማኖቶቻቸውን ጋር በማገናኘት በኢትዮጵያ ውስጥ የሁለቱ ኃይማኖቶች ምዕመናን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 1434 ዓመታት ተከባብረው በሠላምና በፍቅር መኖራቸውን ገልጸዋል። አክለውም ኢሳትን በሁሉም አቅጣጫ በሞራል፣ በማቴሪያል፣ በገንዘብ፣ በሙያ፣ … የመደገፍ የሁላችንም የሕሊና ግዴታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
Ethiopians in Sweden, ESAT fundrise
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ካሪና ሲሆኑ፣ እንዲህ ኢትዮጵያውያን በጋራና በሕብረት የተሰበሰቡበት ዝግጅት ላይ ተገኝተው አብረዋቸው ዕለቱን በማሳለፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ከተለያዩ የኢትዮጵያና የስዊድን አካባቢዎች የመጡትና እንዲህ በጋራ ተሰብስበው ሕብረትና ጥንካሬ ያላቸውን ኢትዮጵያውያኖችን ማየታቸው እንዳስደሰታቸውና ለኢትዮጵያም ቢሆን የሚያስፈልጋት ይኼው ሕብረትና አንድነት እንደሆነ ገልጸዋል። የተሰነጠቀ ዲያስፖራ መኖር እንዳይኖር አሳስበዋል።

የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር እና የአሁኑ የአዲስ ነገር ኦንላይን ድረ ገጽ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ እና በስቶክሆልም የኢትዮጵያ ራዲዮ ኃላፊ አቶ አህመድ ዓሊ የነፃ ሚዲያን ምንነትና አስፈላጊነት በማስመልከት ያዘጋጁትን ጽሑፎች አቅርበዋል።

Tamagne in Sweden for ESAT
ገጣሚ ማትያስ ከተማ (ወለላዬ) ”ዳግም በድል አብራ!” በሚል ርዕስ ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ያዘጋጀውን መወድስ አስደምጧል። ይህ መወድስ ሲነበብ ታዳሚው በሙሉ ከመቀመጫው ተነስቶ ለታማኝ ያለውን አክብሮት በጭብጨባ ገልጿል።

Ethiopian artist Tamagne Beyene in Sweden
በመቀጠልም አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚዲያን አስፈላጊነትና የኢሳትን ሥራ ለታዳሚው እያዝናና አስተምሯል። በኢትዮጵያ የነበሩትና አሁን ያለውን ሥርዓት ምን ይመስሉ እንደነበርና እንደሚመስሉ በቪዲዮ፣ በድምጽና በምስል እና በንግግር በሰፊው ተንትኗል። ይህ የታማኝ ዝግጅት ብዙዎችን ያስደሰተና ያረካ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ አዘጋጅ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ገልፀዋል።



ከፍተኛውን የገቢ ማሰባሰቢያ ገንዘብ ያስገኘው ለጨረታ የቀረበው የሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ምስል ሲሆን፤ ጨረታው ከ500 ክሮነር ተነስቶ በ136 ሺህ የስዊድን ከሮነሩን ተጠናቅቋል። ከዚህ ሌላ በመግቢያ ትኬት፣ በምግብ እና በመጠጥ የተገኘ ገቢ ሲኖር፤ ለጊዜው መጠኑ አልታወቀም። በዕለቱ ምንዛሪ 136 ሺው ክሮነር ከሃያ ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሆነ ታውቋል። በስዊድን የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ እስከዛሬ በአንድ ቀን ካሰባሰቡት የገንዘብ መጠን ውስጥ ይህ የቅዳሜው ዝግጅት ላይ የተሰበሰበው 136 ሺህ ክሮነር ክብረወሰኑን (ሪከርዱን) መያዙን ለመረዳት ችለናል።

በጨረታው ወቅት ብዙዎች በታሰሩት ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ሙስሊሞች ስም ጨረታውን ሲጫረቱ ነበር። ከዚህም ሌላ በታሰሩት ጋዜጠኞች ልጆች፣ በዕለቱ ልደቷን በእስር ሆና በምታከብረው በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ በታማኝ በየነ፣ በጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች ስም ታዳሚዎች በጨረታው ተሳትፈዋል።

ጨረታው ከመጀመሩ በፊት ወ/ሮ መቅደስ ወርቁ ስለአቡነ ጴጥሮስ ታሪክ ያዘጋጁትን ጽሑፍ በንባብ አሰምተዋል።
ጨረታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የስዊድን የኢሳት ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ያላቸውን ሽልማትና ስጦታ አበርክተውለታል። በመቀጠልም አክቲቪስት ታማኝ ዝግጅቱን ላዘጋጁት ወገኖች የሜዳሊያ ሽልማት ሰጥቷል።

ዝግጅቱን በየመሃሉ የተለያዩ አርቲስቶች በባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ ድምቀት ሲሰጡት አምሽተዋል። በመጨረሻም ከአክቲቪስት ታማኝ ጋር ታዳሚዎች የፎቶ ሥነሥርዓት አካሂደው ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ዝግጅቱ ተፈጽሟል። (ይህንን ዝግጅት አስመልክቶ ጠለቅ ያለ ሪፖርት ለማቅረብ እንሞክራለን።)

አክቲቪስት ታማኝ በየነ በአውሮፓ ሰባት ሀገራት ለኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ከስዊድን ቀደም ብሎ በስዊዘርላንድ ተገኝቷል። ከስዊድኑ ዝግጅት በመቀጠል በማግስቱ እሁድ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በኖርዌይ ዋና ከተማ በኦስሎ ወደተካሄደው ዝግጅት አቅንቷል። ከነዚህ ሦስት ሀገራት በተጨማሪ በጀርመን ሙኒክ (ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 16)፣ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም (እሁድ ፌብሩዋሪ 17)፣ በእንግሊዝ ሎንዶን (ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 23) እና በቤልጅየም ብራስልስ (እሁድ ፌብሩዋሪ 24) ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ታውቋል።


አርቲስትና አክትቪስት ታማኝ በየነ በኦስሎ፣ ኖርዌይ (ልዩ አጭር ጥንቅር)
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ ኖርዌይ
የዛሬዋ የእሁድ ምሽት ከታማኝ የኦስሎ የኢሳት ገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር ጋር ያሳለፍኩት ምሽት ነበር። ምንም እንኳን መርሃግብሩን በሙሉ ለመፈፀም ባልችልም የአክትቪስት እና አርቲስት ታማኝን በቪድዮ የተደገፈ ገለፃ ግን ለመከታተል እድሉ ገጥሞኛል።

         ኦስሎ ለኢሳት ገቢ ማሰባሰብያ መርሃግብር ከተገኘው ሕዝብ በከፊል 
ገብስማ ፀጉሩ ከነጭ ሸሚዝ እና ሽሮ መልክ የያዘ ክራቫት ጋር ታማኝን ግርማ ሞገስ አጎናፅፎታል። ታማኝ ወደ መድረኩ ሲመጣ ከታላቅ አክብሮት ጋር ከአምስትመቶ በላይ የሆነው ታዳሚ ከመቀመጫው ተነስቶ ተቀበለው። ታማኝ አፀፋውን እየመለሰ ምስጋናውን ገለፀ። ቀደም ብለው ከጎናቸው ከነበረው ሰው ጋር ይነጋገሩ የነበሩ ሰዎች በፀጥታ ወደመድረኩ ማስተዋል ጀመሩ። ታማኝ ሰላምታውን በአማርኛ ብቻ አልነበረም ያቀረበው ”አሰላም አለኩም” በማለት ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ያለውን አክብሮት ሲገልፅ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተቸረው። ላፕቶፑን አስተካክሎ ከጀርባው በኩል ወዳለው ስክሪን ተመለከተ ትክክል ነው። ንግግሩን ቀጠለ እና እንዲህ አለ-
”ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው በስቶኮልም እና በጄኔቭ ከተመለከትቁት ሕዝብ ኦስሎ ዛሬ የበላይነቱን ይዟል።” ጭብጨባ አጀበው ቀጠለና:-
”…እኔ አርቲስት ነኝ በአርቲስትነት መኖር እችል ነበር። መፅሐፉ የሚለው ከፊትህ ውሃና እሳት ቀርቦልሃል እጅህን ወደወደድከው ጨምር ነው። እኔ እጄን ወደ ውሃ ከትቼ በአርቲስትነቴ እየደነስኩ መኖር አያቅተኝም ነበር። ነገር ግን የእውነት ጉዳይስ? የኢትዮጵያ ጉዳይስ? ዝም ብሎ የሚኖር ህሊና አለን?… እድሜዬ እንደምታዩኝ ላይሆን ይችላል። ፖለቲካ ያቃጥላል፣ ያናድዳል። ሆኖም ግን እስከመጨረሻ ለመፅናት ነው ቃል የገባሁት።”
ቀጠለናም የሙስሊም ወንድሞቻችን ጉዳይ ማንም ችላ ሊለው የማይገባ መሆኑን ”በሰላማዊ መንገድ ‘ድምፃችን ይሰማ’ ማለታቸው እንዴት አድርጎ ነው አሸባሪ የሚያደርጋቸው? ባለፈው የቀረበውን ድራማ አይታችሁታል። አንድ ላይ እኛም ድምፃችን ይሰማ! እንበል” ሲል በአዳራሹ የነበረው ተሰብሳቢ ሁሉ በአንድ ላይ ”ድምፃችን ይሰማ! ድምፃችን ይሰማ!” ሲል አዳራሹን አናወፀው።
በመርሃግብሩ ላይ በቪድዮ የተደገፈው የአቶ ሃይለማርያም እና የአቶ መለስ ተመሳሳይ ንግግሮች በጣም አዝናኝም አስገራሚም ነበሩ። አቶ መለስ በሕይወት እያሉ ለፓርላማ ያደረጉት ንግግር አቶ ሃይለማርያም እንዴት ከአቶ መለስ እረፍት በኃላ እንደደገሙት የሁለቱንም ንግግር እያሳየ አስገረመን። ከሁሉ ያሳቀን ግን ”አቶ ሃይለማርያም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኙት ስም ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” አለና መልሱን መለሰልን።” ባጃጅ ነው የሚባሉት ለምን መሰላችሁ? ባጃጅ ሶስት እግር ነው ያለው አቶ ሃይለማርያምም በሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሚመሩ ባጃጅ ተብለዋል በኢትዮጵያ ሕዝብ… ወደ ስልጣን ሲመጡ ተስፋ ነበረኝ በኃላ ስመለከት ግን በጣም ጎበዝ ኮራጅ ሆኑብኝ አንዳንድ ተማሪ አለ አንዴ አይቶ እጥብ አድርጎ የሚኮርጅ አቶ ኃይለማርያምም አነጋገራቸው፣ ውሃ አጠጣጣቸው፣ እጅ አጣጣላቸው ሁሉ አቶ መለስን ነው የሆኑት።” ሳቅ አጀበው።
አክቲቪስት እና አርቲስት ታማኝ በዛሬው መርሃግብር ብዙ ማለት እንደማይፈልግ ቶሎ ወደ እሳት የገንዘብ ማሰባሰብያ መርሃግብር እንደሚገባ ገትልፆ ንግግሩን ባይገታው ኖሮ ታዳሚው ገና እንዳልጠገበ ከፊቱ ይነበብ ነበር።
በመጨረሻ ግን ታማኝ ዛሬ ካሳየን ፎቶዎች ውስጥ በአድዋ ዘመቻ ጊዜ ዘማች ኢትዮጵያውያን (ክርስትያን እና ሙስሊም ኢትዮጵያውያን) በአራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት ክርስትያኖች ወደ ቤተክርስቲያን ሙስሊሞች ወደ መስጊድ አቅጣጫ ፊታቸውን እንዴት አዙረው ለሀገራቸው ለየ አምላኮቻቸው እንደፀለዩ እና ወደ ውግያው እንደሄዱ በወቅቱ ከነበረው ፎቶ ጋር እያመሳከረ ያሳየን ትእይንት እጅግ መሳጭ እና በመርሃግብሩ የተገኙትን ሙስሊም ወንድሞቻችንን ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን ልብ የገዛ ነበር።
ታማኝ ሲናገር ኢትዮጵያዊነት ውስጡ ይንቀለቀላል። አዎን የፖለቲካ ሰው አይደለም ወይንም ፖለቲካ ሙያው አይደለም። ሀገር መውደድ ግን ሌሎች ፖለቲካን እሳት ብለው ውሃ እየተራጩ ከንፈር ሲመጡ፣ ታማኝ እውነትን ብሎ እጁን እሳት ውስጥ ከቶ ስለ እውነት ለመሞት ቆርጦ የተነሳ ውድ ኢትዮጵያዊ ነው። ”ወይ እስክንድርን ሁን። አለበልዝያ ስሜን መልስ” ነው ያለው ታላቁ እስክንድር አንድ በፍርሃት ሲርድ ላገኘው ወታደሩ። የዛሬዋ የታማኝ ምሽትም ”ወይ ታማኝን ሁኑ አለበለዝያ ስሙን መልሱ” የምታሰኝ ነበረች።






ESAT Kignit Oslo, Norway - Activist Tamagn Beyene Part I, 15 February 2013 Ethiopia

No comments:

Post a Comment