Wednesday, February 6, 2013

ከአቶ ግደይ ዘርዓፅዮን የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ዋና ፀሐፊ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ


የመለስ ሞት በስርአቱ ላይ የአመለካከት ወይም የአሰራር ለውጥን አላመጣም።
  አሁን ያሉት መሪዎች ግን ሥርዓቱን የመለስን ያህል ሊቆጣጠሩት አይችሉም። በውስጣቸውም የመከፋፈልና 
 የስልጣን ፉኩቻ ፈጥሯል። ይህ ሁኔታ ለትግላችን አንዳንድ ቀዳዳዎችንና አመቺ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል።
 አቶ ግደይ ዘርዓጽዮን


በጀርመን ሀገር በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመውጥላመጽሔት በአንደኛ ዓመት ቁጥር አምስት ዕትሙ ከአቶ ግደይ ዘርዓፅዮን ጋር ቃለምልልስ ያደረገ ሲሆን፤ ሙሉ ቃለምልልሱን ከዚህ በታች ያገኙታል።

የዛሬው የጥላ አንደኛ ዓመት ልዩ የክብር እንግዳ አቶ ግደይ ዘርዓፅዮን ይባላሉ። አቶ ግደይ ህወሓትን ከፈጠሩት ጥቂት ግለሰቦች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። እሳቸው ታዲያ እስካሁን የእድሜያቸውን ሁለት ሶስተኛ በኢትዮጵያ ትግል ውስጥ በማሳለፍ ላይ ናቸው። አገራችን ውስጥ ባላቸው የፖለቲካ ህይወት ልምድ ከጠገቡትና አንቱ ከሚባሉት በጣም ጥቂት ሰዎች መካከልም እጅጉን ቦታ የሚሰጠው ስፍራ አላቸው።

የቀድሞውን የፊውዳል ሥርዓት ከመቃወም ጀምሮ ደርጉንም በማፍረክረክ ከተሰሩት ታሪኮች አብዛሃኛው ላይ የእሳቸው አሻራ አለበት። የተወለዱት በፈረንጅ አቆጣጠር 1950 .. ነው። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮችም አድገዋል። ተምረዋል። በቀድሞው አፄ ኃይለሥላሴ/የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እአአ 1968 – 1974 .. ቆይተዋል። በተለያዩ ክልሎች ማደጋቸውና መማራቸውም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቀላሉ ለመረዳትና ብሔራዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰው እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ብዙዎች ይስማማሉ። የተለያዩ የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ብዙዎች መፅሃፍ ሲያገላብጡ ጊዚያቸውን ከማጥፋት ይልቅ አቶ ግደይ ጋር በመደወል ወይም በአካል በመገናኘት የካበተ ልምዳቸውን በማስረጃ አስደግፈው ማግኘት እየቀለላቸው ከመጣ ውሎ አድሯል። ህወሓትን ከፈጠሩት ጥቂት ግለሰቦችም መካከል አንዱ ናቸው። ከህወሓት ጋር በደርጉ ዘመን ከተለያዩ በሁዋላም ከአገር በመውጣት በተቃዋሚው ጎራ ተሰልፈው በመታገል ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የተቃዋሚውን ጎራ ባንድ ጥላ ለማሰባሰብና ጠንካራ ኃይል ለመሆን በቅርቡ ከስምንት ፓርቲዎች ተውጣጥቶ የተቋቋመውንየኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎበዋና ፀሐፊነት በመምራት ላይ ናቸው።

እኛም ወቅታዊውንና ያለፈውን ታሪክ እያጣቀሱ ለአንባብያን በቂ እውቀት እንዲያስጨብጡልን ከሚገኙበት ከኖርዌይ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርገናል። ጠቃሚ መረጃዎች ከተካተቱበት ከዚህ ውይይት በርካታና ሁለገብ መረጃዎች እንደምታገኙ እምነታችን ነው። ቃለ-ምልልሱን ጋዜጠኛ መስፍን ኣብርሃ አዘጋጅቶታል። መልካም ንባብ!

ጥላ፦ ህወሓትን ከመመስረታችሁ በፊት ማገብትን መስርታችሁ ነበር። እርሶ ደግሞ ሁለቱንም ድርጅቶች ከፈጠሩት ጥቂት ሰዎች አንዱ ነዎት ዛሬ ደግሞ ሌላ ካምፕ ውስጥ ነው የሚገኙት። የፈጠሩትን ድርጅት መልሶ መቃወም አይፈታተንም ወይ?

አቶ ግደይ፦ እርግጥ ማገብትንና ከዝያም ቀጥሎ ህወሓትን በመመስረት ከጀማሪዎቹ አንዱ ነኝ ሆኖም ድርጅቱ ከተመሰረተበት ዓላማና አሰራር ውጭ ሲሆን እስካላመንኩበትና እስካልተቀበልኩት ድረስ የፈጠርኩት ስለሆነ አብሬ የሙጥኝ ማለት ትክክል አይደለም። ኅሊናየ ቀናና ትክክል ነው ብሎ በሚያምንበት መስመር ላይ እስከቆምኩ ድረስ ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም ዝግጁ ነኝ። በእምነቴ ብቻየን የምቆምበት ጊዜ በህይወቴ ብዙ ጊዜ አጋጥሞኛል ሆኖም ትክክልነታቸው በጊዜ እየተረጋገጠ ሲመጣ ሁላችንም እንማርበታለን እኔም እረካበታለሁ። አቋሜ ትክክል በማይሆንበት ወቅትም ከድክመቴ እማርበታለሁ የሚል እምነት አለኝ። ከሁሉም በላይ ግን ልዩነትን ማክበር ዲሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብት ስለሆነ የኅሊና እረፍት ይሰጠኛል።

ጥላ፦ ገና በአፍላነት ዕድሜያችሁ የማይገፋ የሚመስለውን ተራራ ለመናድ ዓላማ ሰንቃችሁ ድርጅት መስርታችሁ ወደ ትግል ገብታችሁ እልፎችን ካሰለፋችሁና ከመራችሁ በሁዋላ ከእናነተ በሁዋላ በመጡ ሰዎች ከፈጠራችሁት ድርጅት እንዴት ለቀቃችሁ?በእውነት ከእነመለስ ቡድን ጋር ያለያያችሁ ትክክለኛ ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ግደይ፦ እኔና ዶክተር አረጋዊ ከድርጅቱ የለቀቅነው በፖለቲካ ሴራ ነው። በሴራው ከኛ በኍላ የመጡት ብቻ ሳይሆን ከኛ ጋር መስራች የነበሩት እነ ስዩም መስፍንና አባይ ፀሐየም አሉበት፣ ከነዚሁ ጋር የሴራው ዋና መሪዎች ስብሓት ነጋ፣ ስየ አብረሃና መለስ ዜናዊ ናቸው። መነሻው የስልጣን ፍላጎት ሲሆን ከኔ ጋር ለነበረው ልዩነት የፖለቲካ ልዩነት በሚል እንደሽፋን ተጠቅመውበታል። የተነሱት ፖለቲካዊ ልዩነቶች ኣንዳንዶቹ ወቅታዊ ያልሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የማያምኑበትን ግን ከኔ ጋር ልዩነት ለመፍጠር ሆን ብለው የተወሰዱ አቋሞች ነበሩ። የስታሊንና የሆጃ ተከታዮች በመሆናቸው የዲሞክራሲን ጥያቄ አስመልክቶ ከኔ ጋር ትልቅ ልዩነት ነበር። ሌላው ልዩነታችን በታክቲክና በስትራተጂ ያለው ግኑኝነት በሚመለከት ሆኖ በተግባር ሲተረጎም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በኢትዮጵያውያን ታጋይ ኅይሎች የግንባር ጥያቄ በሚመለከት፣ ከህዝባዊ ግንባር ጋር የነበረ ግኑኝነት በሚመለከት የመሳሰሉ ነበሩ። ይህም ቢሆን እነ መለስ እየተውላገዱም ሆነ እየተደናበሩ እኔ ያልኩትን አመለካከት እየተከተሉ በመሄዳቸው በየጊዜውግደይ የሚለው ይህን አልነበረም ወይየሚለው ጥያቄ እየተነሳ ያስቸገራቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ጉዳይ ሰፊ ስለሆነ በዚሁ ቃለመጠይቅ ለመዘርዘር አስቸጋሪ ይሆናል። በዚሁ ላይ የጻፍኳቸው ጽሁፎች በእጅ የተጻፉና በትግርኛ ስለሆኑ ለአንባቢያን በስፋት ለማቅረብ ጊዜ አላገኘሁም።

ጥላ፦ እነሱ የእናንተ ሃሳብ ተራማጅ ያልሆነ ስለነበር በውይይቱ ወቅት ሃሳባችሁ ተሸንፎ በክብር እንዳሰናበቷችሁ ነው የሚናገሩት። እርሶ ምን ይላሉ?

አቶ ግደይ፦ ይህ ውሸት ነው እርግጥ አልገደሉኝም አላሰሩኝም የነበረው ሁኔታ ግን በጣም አስጊና ኢዲሞክራሲያዊ ነበር። ከትግርኛ ጽሁፎቼ አንዱ የሚከተለውን ብትመለከቱ ሁኔታውን በስፋት ይገልጸዋል፣ http://www.tand-tesfana.webs.com/Ghidey-MLLT2.pdf

ጥላ፦ በወቅቱ ከህወሓት ጋር ሲለያዩ ምን ነበር የተሰማዎት?የታጋዩ ስሜትስ ምን ነበር?

አቶ ግደይ፦ ህወሓት በስልጣን ሽኩቻና በተሳሳተ መስመር መግባቱ በጣም ነበር ያሳዘነኝ። ካድሬውም የተፈጠረውን ሁኔታ ለመገንዘብ አለመቻሉና ፈሪ መሆኑን ስገነዘብ ለዚሁ ድክመት ከተጠያቂዎቹ አንዱ መሆኔንና የሰራነውስ ድክመት የቱ ላይ ነው የሚለውን እንድመለከት አድርጎኛል። በዚሁ ጉዳይ ታጋዩ እንዳዘነና እንዳልተቀበለው እስካሁንም ድረስ በተለያዩ መልክና ሁኔታዎች ጥያቄ እያነሳባቸው መሆኑ የሚታይ ሃቅ ነው።

ጥላ፦ እናንተ ከምስረታው ጀምሮ የታገላችሁለት ህዝባዊ ዓላማ እንዴት ተጓዘ?አሁን የደረሰበት ደረጃስ የታገላችሁለት ነበር ወይ?ምን ጎደለው?

አቶ ግደይ፦ ህወሓት ትግሉን ሲጀምር በወቅቱ ሲነሱ የነበሩትን ጥያቄዎች የብሄሮች እኩልነት፣ መሬት ለአራሹ፣ የዲሞክራሲ መብቶች የመናገር የመጻፍ የመደራጀት፣ የዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት፣ የሚሉትን አንግቦ የደርግን ወታደራዊ መንግስት በትጥቅ ትግል ለመጣል ነበር የተሰለፈው። 1984 እኔ እስክለቅ ድረስ ህዝብን በማደራጀት ሰፊ ነፃ መሬት በማውጣትና አስተዳደሮችን በመመስረት፣ የህወሓት ሰራዊት ደግሞ ከደባይና ከተከላካይ ደርጃ ወጥቶ ወደ አጥቂነት የተሸጋገረበት ደርጃ ላይ ደርሶ ነበር። በመጨርሻም ደርግን አሸንፎ ስልጣን ይዟል። የተነሳንባቸውን የብሄሮች እኩልነትና የዲሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት ጥያቄ ግን አላሟላም ብቻ ሳይሆን ጨቋኝና አፋኝ የሆነ የጠባብ ብሄርተኛ ሥርዓት መስርቷል።

ጥላ፦ ህወሓት ከትግሉ ጀምሮ ዴሞክራቲክ ነበር ወይ? በድርጅቱ ውስጥ ጤናማና የተስተካከለ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አካሄድ ነበር ማለት ይቻላል?

አቶ ግደይ፦ ትግሉ ሲጀመር ሁሉም የሚተዋወቅና የተማረ ስለነበር ውይይትም ውሳኔዎችም በግልጽና በጋራ አመራር የሚወሰኑ ፍራቻ የሌለበት ዲሞክራቲክ ነበር። ዲምክራቲክና ሰብአዊ መብቶች አመልካከታችን በማርክሲስት ሌኒንስት ስነሃሳብ የታጀበ ስለነበርና በህብረተሰባችን የነበረን ተሞክሮ ጋር በማዛመድ የቱን ያህል ብስለትና ዲሞክራሲያዊ ባህል ነበረው የሚለው ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። ድርጅቱ እያደገ ሲሄድና በትግልም እያጋጠሙት በሄዱት ችግሮችና ኢንዲሁም ወታደራዊ ድርጅት በመሆኑ ወታደርዊ ዲሲፕሊን እየገዛው በመሄዱ የነበረው ዲምክራቲክ ሁኔታ እየተሸረሸረ መሄዱን እናያለን። ይህንን በሚመለከት በስፋት እላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ ላይ ገልጫለሁ።

ጥላ፦ በትግሉ ወቅት በተለይ 72/73 .. አንዳንድ የሰራዊቱ አመራሮች ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ ተግባርን ይፈፅሙ ነበር። ይህም ተራውን ተዋጊ በዱላ መቀጥቀጥና በገመድ የማሰር የሃሳብ ልዩነት ያለውን እንደ ሰላይ በመቁጠር እርምጃ የመውሰድ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ይፈፀሙ ነበር። እንደ ድርጅቱ የወቅቱ መሪ ይህን ለማስቆም ምን አድርገዋል? ምክንያቱም አንዳንድ ፀሐፊዎች ጣታቸውን ከድርጅቱ ወደ ተለያያችሁት የወቅቱ አመራሮች እየቀሰሩ ነውና።

አቶ ግደይ፦ እንደዚህ ዓይነቱ አሰራር በድርጅቱ ሕግ የተከለከለ ነው ያስቀጣልም። ማንኛውም ታጋይ የዚህ ዓይነት ጥፋት ሲታይ ለበላይ መሪዎች የማመልከት መብት አለው። በተለያዩ ወቅት የተለያዩ ዝንባሌዎች የታዩበት ሁኔታ አለ። በስፋት የታዩ ዝንባሌዎች እንደ ወታደርነትና መኮንነት የመሰሉትን በዘመቻ ለማረም የተሞከረበት ወቅት አለ። ይህን ዝንባሌ ስንመታ በፖለቲካ ዲፓርትመንት የነበሩትን የነመለስን ተክለሰውነት ማጠናከርና የሴራ ካድሬዎቻቸውን እንዲያሰለጥኑበት እድል ከፈተ። በሰራዊት መሪዎች በተለያየ ወቅትና ቦታ የተደረጉትን ጥፋቶችን ለማወቅ አልችልም፣ በቀጥታ የዚህ ዓይነት ጥፋት ተፈጽሟል የሚል ሪፖርት ከደረሰኝ ግን በድርጅቱ ሕግ መሰረት ቅጣት ወይም ተግሳጽ እንደምሰጥ አልጠራጠርም።

ጥላ፦ በትግሉ ወቅት ኢህአፓ ያቀረበውን የህብረት(የትግል) ጥሪ ህወሓት ያላስተናገደበት መሰረታዊ ጉዳይ ምን ነበር? አንዳንዶች በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የነበረው የትምክህትና የጥበት አመለካከት ችግር ነው ይላሉ። እርሶስ?

አቶ ግደይ፦ ኢህአፓ ሶስት ደረጃ ያለው የህብረት ጥሪ ነበረው 1ኛው በኮምኒስት ፓርቲ ለተደራጀ ስትራቴጅክ የሚሉት፣ 2ኛው ለህዝባዊ ዲምክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ለሚታገሉት ዲምክራሲያዊ ግንባር የሚሉት 3ኛው ደግሞ ዲሞራሲያዊ ጥያቄ አንስተው ለሚታገሉት የጋራ ትብብር የሚሉት። በህወሓት እምነት ለህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚታገል በሁለተኛው የኢህአፓ መመዘኛ የምታገል ነኝ ሲል ኢህአፓ አልተቀበለውም ምክንያቱም ህወሓት የኮሚኒስት ፓርቲ አመራር የለውም በሚል። በተጨማሪም ኢህአፓ የብሄር ትግል የዲሞክራሲ ጥያቄ ቢሆንም የሰራተኛውን የጋራ ትግል ያደናቅፋል የሚል አመለካከት ነበረው። በአንጻሩ ህወሓት የብሄር ጥያቄ በአሁኑ ወቅት ጎልቶ የሚታይና ህዝቡንም በቀላሉ ሊያነሳሳ የሚችል ስለሆነ በሰራተኛው ፓርቲ እየተመራ የሰራተኛውን ትግል ሊያጎለብት ይችላል የሚል አመለካከት ስለነበረው የኢህአፓን አቋም እንደንቀት ስላየው የቀረበለትን ሶስተኛውን አማራጭ አልተቀበለውም። ህወሓት ሶስተኛውን አማራጭ አለመቀበሉ ስህተት ነበር። በመጨረሻም ሁለቱም ድርጅቶች የተለያዩትየማንኛችን ሂደት ትክክል ስለመሆኑ ጊዜ ይፈርደናልበሚል ለግጭት በር በከፈተ መንገድ ነበር። ሂደቱም ያሳየን ይህንኑ ነው።

ጥላ፦ ከኤርትራ የወቅቱ ተዋጊዎች ከነበሩት ሻዕቢያ፣ጀብሃ ወዘተ ጋር ህወሓት መስርቶት የነበረው ግንኙነት የጌታና የሎሌ አይነት ነው ብለው የሚከራከሩ ፀሃፍት አሉ። የእርሶስ እምነት ምንድን ነው?

አቶ ግደይ፦ ይህ አቀራረብ ከእውነቱ በጣም የራቀ ነው። በአብዛኛው ከኤርትራ ድርጅቶች ጋር የነበረው ግንኙነት የግጭትና አለመስማማት ሂደት ነው። ይህን ስል ግን የተጋገዙበትና የተባበሩበት ሁኔታ አልነበረም ማለት አይደለም።

ጥላ፦ ህወሓትን በመፍጠር ባካሄዱት ትግል ይፀፀታሉ ወይ?ተቆጭተውስ ያውቃሉ?

አቶ ግደይ፦ በወቅቱ በነበሩት አንገብጋቢና ዲምክራሲያዊ ጥያቄዎች ተነስቼ የብሄርን ጭቆና ለመታገልና በዚያውም በኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ ከሚታገሉት ሌሎች ኃይሎች ጋር ሆኖ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት በሚል ዓላማ ህወሓትን መፍጠሬና መታገሌ አይጸጽተኝም። የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር ግን ይህን ታላቅ የህዝብ ትግል ተገቢውን አመራርና አሰራር ሳንሰጥ ቀርተን ተመልሶ ህዝቡን የሚጨቁንና አገሪቱንም ሊበታትን የሚችል ሥርዓት መፍጠራችን ነው። ይህ እንዳይሆን ምን ሊደረግ ይችል ነበር ለሚለው ሰፊ ጥናትና ውይይት የሚያስፈልግ ሲሆን በበኩሌ አጠር ባለ መንገድ የሚከተሉትን ዘርፎች ማየት ይቻላል፣ አንደኛ የድርጅት ውስጣዊ ዲሞክራሲያዊ አሰራርንና በህብረተሰቡ የሚመሰረተው ዲሞክራሲያዊ መዋቅር በሚመለከት፤ ሁለተኛ በኢትዮጵያ ደረጃ የሚደረገውን የጋራ ትግል ትኩረት መስጠትን በሚመለከት፤ ሶስተኛ ከሌሎች ዲምክራሲያዊ ኃይሎች ጋር የሚፈጠረው አለመግባባት አፈታትን በሚመለከት ቀደም ተብሎ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባ ነበር እላለሁ።

ጥላ፦ በስደት በቆዩባቸው ሶስት አሰርት ዓመታት ያካሄዱት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ግደይ፦ ህወሓትን ለቅቄ የወጣሁት 1987 . ነው። ከወጣሁ ጀምሮ የህወሓትን የተሳሳተ መስመርና - ዲሞክራሲያዊ ተፈጥሮ እንዲሁም በህዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ግፍና በደል በግልም ሆነ በመደራጀት እየታገልኩ ነው። 1995 .. ጀምሮ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ትዴት (Tigray Alliance for National Democracy TAND) ከሚባለው ድርጅት ጋር ተሰልፌ የትግራይ ህዝብ ያለውን ሥርዓት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመተባበር እንዲታገልና በጋራ ዲምክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰርት እየታገልኩ ነው። በተጨማሪም ትግሉን ከሌሎች ዲምክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በማስተባበርና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እንዲተባበሩና በጋራ እንዲታገሉ በማድረግ ትዴት የበኩሉን አስተዋጾ በማድረግ ላይ ነው።

ጥላ፦ በስደት የሚገኘው ህዝብ በተቃዋሚ ኃይሎች የእርስ በርስ መጠላለፍ ፈጣን ለውጥ ባለማየቱ ተስፋ የመቁረጥ ነገር ይስተዋልበታል። መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ ግደይ፦ እርግጥ የድርጅቶች እርስ በርስ መጠላለፍና የአመራር ድክመት መታየቱ የህዝቡን የትግል ስሜት እንዲዳከም እንዳደረገው አያከራክርም። ለትግል የገፋፉን ሁኔታዎች ማለት የዲሞክራሲ እጦት፣ የፍትህ መጥፋት፣ በጠባብ ብሔራዊ እምነት የሚደረግ አድልዎና ግፍ፣ የኑሮ ችግር፣ ብኩንነት፣ ጭቆና ወዘተ እስካሉ ድረስ ትግሉ አይቆምም። ስለሆነም ተስፋ ቆርጦ ከትግል መሸሽ ሳይሆን ያለን አማራጭ ድክመታችንን አርመን በተሻለ መንገድ መታገል ብቻ ነው። ለዚሁም ከስምንት ወር በፊት የተለያዩ ድርጅቶችን አሰባስቦየኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎበሚል ስም የተደራጀውና የትግል አማራጭና አቅጣጫ ይዞ የቀረበው ጥሩ አብነት ሊሆን ይችላል፣ የተጠቀሱትን የተቃዋሚ ኅይሎች ድክመት ያስወግዳል የሚል እምነትም አለኝ።

ጥላ፦ እንደገለፁት በቅርቡ የተቃዋሚውን ኃይል በአንድ ጥላ ስር የማሰባሰብ ከፍተኛ ስራ ላይ ተጠምዳችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ መስርታችሁዋል። እስካሁን የሸንጎው እንቅስቃሴ ምን ውጤት አስገኝቷል?

አቶ ግደይ፦ ሸንጎ ከተመሰረተ 8 ወር ገደማ ሆኖታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ድርጅታዊ መዋቅርን መቅረጽና ማጠናከር፣ ሸንጎን ለማስተዋወቅ በተለያዩ ትልቅ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎች ማካሄድና በሚድያ መግለጫዎችን በመስጠት፣ ደጋፊ ኮሚቴዎችን በተለያዩ ከተሞች ወይም አገሮች ማቋቋም፣ ከሌሎች ዲምክራሲያውያን ኅይሎች ጋር ትብብር እንዲፈጠር ጥረት በማድረግ ሌሎች 8 ድርጅቶች የሚሳተፉበት የጋራ የትብብር መድረክ በመፍጠርና በመሳተፍ፣ በዲፕሎማሲ ስራ በአሜርካና አውሮጳ ለሚገኙ አንዳንድ የመንግስታት መስሪያ ቤቶች ግኑኝነት በመፍጠር ዓላማውንና የኢትዮጵያን ሁኔት ማስረዳት፣ የመሳሰሉትን ሰርቷል። ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት የሽንጎን ድህርገጽ http://www.ethioshengo.org/ መመልከት ይቻላል።

ጥላ፦ ሸንጎው በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎችን የማካተት ዓላማ አለው ወይ?ያደረጋችሁት ጥሪ ነበር? ምላሹስ ምን ይመስላል?

አቶ ግደይ፦ የሸንጎ ዓላማ ሁሉም ለዲሞክራሲ የሚታገል ኅይል አገር ቤት ይሁን ውጭ፣ በትጥቅ ትግል ይሁን በሰላም የሚታገለውን ሁሉ በጋራ በመቆም እንዲታገልና ያለውን ሥርዓት አስወግዶ በዲምክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን ለህዝብ የሚሸጋግርበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ነው። ስለሆነም አሉ የተባሉትን ታጋይ ኃይሎች ለማገናኘት ሞክሯል። አገር ቤት ካሉት ታጋዮች ጋር በግልጽ ሊደረግ የሚችል ግንኙነት አሁን ያለው ሁኔታ አያመችም። ትግሎቻችንን ግን ማቀናጀት እንችላለን። ዋናው የትግል ሜዳ በአገር ውስጥ መሆኑን እንገነዘባለን። አገር ቤት ያለው ስርአቱን ፊት ለፊት በመጋፈጥ መስዋዕትነትን ሲወስድ በውጭ ያለው ደግም ለትግሉ ደጋፊ የሆኑትን የዲፕሎማሲ፣ የገንዘብና የማቴሪያል ካስፈለገም የትጥቅ፣ የሚድያ፣ የምልመላ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል። ሌላው ላስታውስ የምወደው ሸንጎ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ድርጅቶች የራሳቸው መዋቅር አገር ቤት እንዳላቸውም ጭምር ነው።

ጥላ፦ የሸንጎው ግብ ምንድን ነው?

አቶ ግደይ፦ የሸንጎው ዓላማዎችና ግብ የሚከተሉት ናቸው።
1/- በኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና ሉዓላዊነት፣እንዲሁም በአገሪቱ የግዛት አንድነት ላይ ግልጽና የማያወላውል እምነትና አቋም መያዝ፣
2/- የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣በየድርጅቶች ውስጥና በምንሰባሰብበት የህብረት ማዕቀፍ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ግንኙነቶችንና አሠራሮችን በማስፈን መስራት፣
3/- በኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ፀንቶ መታገል፣
4/- በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ምንም አይነት አድሎ እንዳይኖር ሁሉም ዜጋ እኩል መሆኑን ማመንና በተግባርም ማረጋገጥ፣
5/- የህወሃት/ኢሕአዴግ መንግሥትና ሥርዓት የአፈናና የጭቆና ሥርዓት በመሆኑ መለወጥና በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መተካት እንዳለበት ማመን፣ በተጠቀሱት ዓላማዎች ዲሞክራቲክ ኃይሎችን በማሰባሰብና በጋራ በመታገል ያለውን ሥርዓት አስወግዶ ሁሉንም በዲሞክራሲያው መንገድ ሊያሳትፍ የሚችል የሽግግር መድረክ ተፈጥሮ ዲሞክራሲያዊ መድብላዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ነው።

ጥላ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት የሸንጎውን ግብ ከማሳካት አኳያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

አቶ ግደይ፦ የመለስ ሞት በስርአቱ ላይ የአመለካከት ወይም የአሰራር ለውጥን አላመጣም። አሁን ያሉት መሪዎች ግን ሥርዓቱን የመለስን ያህል ሊቆጣጠሩት አይችሉም። በውስጣቸውም የመከፋፈልና የስልጣን ፉኩቻ ፈጥሯል። ይህ ሁኔታ ለትግላችን አንዳንድ ቀዳዳዎችንና አመቺ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል።

ጥላ፦ በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሸንጎው እንዴት ይገመግመዋል?

አቶ ግደይ፦ ይህንን በሚመለክት ሸንጎየኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና የሸንጎው የትግል አቅጣጫየሚል ሰፊ ጽሁፍ አውጥቷል ይህንን ማጣቀሻ በሚቀጥለው አድራሻ መመልከት ይቻላል፣ http://www.ethioshengo.org/files/ARCHIVE/Road_Map_A.pdf .

ጥላ፦ የኢትዮጵያ ህዝብ በኑሮ ውድነት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለመስፈን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በግዳጅ የገዢው ፓርቲ አባልነት እየተማረረ ይገኛል። ግን በሥርዓቱ ላይ የተደራጀ ተቃውሞን ሲያሰማ አይታይም። ችግሩ ምንና የማን ነው ይላሉ?

አቶ ግደይ፦ የህወሓት/ኢህአዴግ ስርአት አፋኝ በሆኑ አሰራሮችና ህጎች እንዲሁም ጨካኝ በሆኑ እርምጃዎች ተቃዋሚ ድርጅቶችና ህዝቡ እንዲዳከሙና እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ከታሪክ እንደምንማረው ማንኛውም ጨቋኝ ስርአት ለአጭር ጊዜ እድሜውን ሊያራዝም ካልሆነ በስተቀር ጭቆናና ብሶት እስካለ ድረስ የህዝቡን መነሳሳትና መታገል ሊያግደውና ሊያስቀረው እንደማይችል ነው። ተቃዋሚ ኃይሉ ይህንን ለመመከት የሚያስችል ዘዴዎችን መፍጠር ግዴታ አለበት። 1 5 የሚለው የህወሓት/ኢህአደግ አሰራር ህዝቡን እንዳይላወስ ያደረገ አልቅስ ሲሉት እንዲያለቅስ፣ በግድ ምረጥ ሲሉት እንዲመርጣቸው፣ ሰላማዊ ሰልፍ ውጣ ሲሉት እንዲወጣ፣ ወዘተ አድርጎታል። የህዋሱ መሪ ካድሬዎች በጥቅም የተደለሉ አብዛኞቹ በመንግስት መስሪያ ቤቶችና ፕሮጀክቶች የሚሰሩ ናቸው። የተቀሩት አባሎች ደግሞ ከስራ እንዳይባረሩ ወይም ተመሳሳይ ጥቅም እንዳይነፈጉ ወይም እርምጃ እንዳይወሰድባቸው ፈርተው አጎንብሰው ያገለግላሉ ወይም ይኖራሉ። ተቃዋሚው ይህንን ህዋስ ማፍረስ አለበት። ለነገሩ ህዝቡም ብሶቱ እየጨመረ ሲሄድ ራሱ እያፈረሰው ይመጣል።

ጥላ፦ በሥርዓት ለውጡ ላይ የህዝብና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ምን ይሆናል?

አቶ ግደይ፦ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝቡን ትክክለኛና ወቅታዊ አመራር በመስጠትና በማደራጀት ሲታገሉ ህዝቡም ለጥሪያቸው ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በትግሉ መሳተፍን ይጠይቃል። መታገል ሲባል በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በንብረት፣ በሂወት፣ በችሎታ መሳተፍን የመሳስሉ ናቸው። በትግል ፓርቲና ህዝብ ተብሎ ተለያይቶ የሚሄድ ነገር አይደለም ሁለቱም አስፈላጊዎችና ተጣምረው መጓዝ አለባቸው።

ጥላ፦ የሚዲያውስ?

አቶ ግደይ፦ ሚድያ ያለውን እውነታ ለህዝብ በማቅረብ የስርአቱን ምንነትና የአገሩን ሁኔታ እንዲያውቅ አገሩንና ጥቅሙን እንዲጠብቅ የሚያስችል አካል ነው። ጨቋኝ ስርአቶች በቅድሚያ የሚቆጣጠሩትና የሚያፍኑት ነፃ ሚድያን ነው። ከዚህም አልፈው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ለማሰራጨት ይጠቀሙበታል። በኢትዮጵያ ያለውም ሁኔታ ይኸው ነው። ነፃ ሆነው ሊሰሩ የሚችሉ ሚድያ በውጭ ያሉት ናቸው። ህዝባችን ያለውን ያገራችን ሃቅና ሁኔታ በማቅረብ ህዝቡ እንዲማርና እንዲያውቅ በማድረግ ያለውን ሥርዓት እንዲታገል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

ጥላ፦ አቶ ግደይ ዘርዓፅዮን ስለሰጡን ማብራሪያ በአንባብያን ስም ከልብ እናመሰግናለን።
አቶ ግደይ፦ እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ። በርቱ!!

No comments:

Post a Comment