Sunday, February 3, 2013

ከአቶ መለስ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ጋር አልስማማም፤ እናም አላስቀጥልም

“If liberty means anything at all, it means the right to tell people what they do not want to hear” - George Orwell

 (ከግርማ ሰይፉ) girmaseifu32@yahoo.com
ጥር ዘጠኝ ቀን የነበረው የፓርላማ ውሎ ሁለት መልክ የነበረው ነው፡፡ አንደኛው ያለወትሮ ፓርላማው ከመንግስት የቀረበለትን ሞሽን በጥቂት ድምፆችም ቢሆን የተቃውሞ ድምፅ እና ድምፀ-ተአቅቦ ያስመዘገበበት ነበር፡፡ ጥሩ ፍንጭ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በኩል የተለየ ሃሳብ ለምን ሰማው በሚል በእኔ እና በወከልኩት ድርጅት ላይ ፀረ-ህዝብ የሚል ፍረጃ ለማድረግ በፍፁም ያልሳሱበት ነበር፡፡ በምክር ቤት ውስጥ ያቀረብኩትን ሃሳብ እንደወረደ ለአንባቢ አቀርበዋለሁ፡፡
በቅድሚያ የአንድ አገር መሪ ለነበረ ሰው በህይወት እያለ በመንግስት ሀላፊነቱ ወቅት የሚመለከታቸውን የተለያዩ ክፍተቶች ወይም ሊያስቀጥላቸው የሚፈልጋቸው የተለያዩ አስተሳሰቦች ካሉት እነዚህን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ፋውንዴሽኖችን ማቋቋም የተለመደ በመሆኑ በመሰረተ ሃሳቡ ችግር የለበትም የሚል እምነት አለኝ። በዓለም የሚታወቁ በርካታ የአገራት መሪዎችም የዚህን አይነት ተቋም መስርተው ይንቀሳቀሳሉ። አብዛኞቹም ከአገራቸው አልፈው በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ጠቃሚ የሆኑ አገልግሎቶችን የሚሰጡበት ሁኔታ ይታያል። ስለዚህ በመርህ ደረጃ በፋውንዴሽኑ መቋቋም ላይ በግሌ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ቢሆንም መቋቋም ያለበት ግን መንግስት እንደነዚህ አይነት ተቋማትን ወይም ፋውንዴሽኖችን በአዋጅ በመመስረት መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም እንዲህ አይነት ፋውንዴሽኖች የሚቋቋሙበት የራሱ ስርዓት አለው። ለምሳሌ አዋጅ ቁጥር 621/2001 እንዲህ አይነት ፋውንዴሽን ማቋቋሚያን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች አሉት። ስለዚህ ይህ ፋውንዴሽን መቋቋም ያለበት በዚህ አዋጅ ስር መሆን አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን ፋውንዴሽኑ መቋቋም ያለበት በመንግስት ሳይሆን በአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦችና በአድናቂዎቻቸው ነውየሚል አቋም አለኝ ነው ያልኩት፡፡

ይህ ሃሳብ እንዴት አድርጎ አንድን የምክር ቤት አባልና የወከለውን ድርጅት ፀረ-ህዝብ ሊያሰኝ እንደሚችል አይገባኝም፡፡
በማስከተልም ረቂቅ አዋጁ በማብራሪያው

  •  አቶ መለስ ያወጧቸውን ስራዎች እና ራዕያቸውን ከህልፈታቸው በኋላም ቢሆን በፅናት ልናስቀጥላቸው እንደሚገባ በተመሳሳይ ሁኔታ ህዝብ በአንድ ቃል ገልፆታልየሚለው ትክክል እንዳልሆነ፤ ህዝብ የሚባለው የኢህአዴግ አባልና የእርሳቸው ደጋፊ ብቻ ነው ካልተባለ በስተቀር ለዚህ ሀሳብ እውቅና እንደማልሰጥ፤ እኔም ለምሳሌ በእርሳቸው ፍልስፍና ብስማማ ኖሮ የኢህአዴግ አባል እሆን እንደነበር፤ የልማታዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስት የሚባል ፍልስፍናን ማስፋፋት ሳይሆን መለወጥ እንደምፈልግ በምክር ቤት የምገኘውም ይህንን ተግባር ለመወጣት እንደሆነ ለምክር ቤቱ አስመዝግቤያለሁ፡፡
  • ይህንን መነሻ አድርገን ስንወስድ መንግስት ማለት የአቶ መለስ ደጋፊዎችም ተቃዋሚዎችም አስተዳዳሪ በመሆኑ ይህ አስተሳሰብ እንዲቀጥል የማይፈልጉ ሰዎች የሚከፍሉትን ታክስ ለዚህ ተግባር ማዋል ተገቢ አለመሆኑን፤ በዚህ ከቀጠልን ሌሎች የተቋቋሙና የሚቋቋሙ ፋውንዴሽኖች ለምሳሌ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፤ የፕሮፌሰር አክሊሉ ፤ ወዘተ እያለን በጀት ልንበጅት ስለሚሆን እራሳቸውም አቶ መለስም በህይወት ቢኖሩ ይህን እንደማይደግፉት፤
  •  ለፋውንዴሽን የጠቅላላ ጉባዔ አባልነት የተመረጡ የመንግሰት መስሪያ ቤቶች ዝርዝር በፍፁም ተገቢ እንዳልሆነ እና የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መሆን ያለባቸው ለፋውንዴሽኑ በገንዘብ በዕውቀትም ከፍተኛ አሰተዋፆኦ የሚያደርጉና ወደፊትም ማድረግ የሚፈልጉ እንዲሁም ለፋውንዴሽኑ ማደግ ተግተው የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው፤
  •  ለዚህ ፋውንዴሽን የተለየ ተብሎ የተሰጠው የቀረጥ ነፃ መብት ፋውንዴሽኑ ለስራ ማስፈጸሚያ ወደ አገር የሚያስገባቸው እቃዎች፣ መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ይሆናሉ፤ይላል። ይህም ከውጭ የሚመጣው ነገር ሁሉ ካለምንም ቀረጥና ታክስ እንዲገባ መደረጉ ይህንን ፋውንዴሽን ለሚመሩት ሰዎች ቀዳዳ እንደሚከፍት ግልፅ ነው ታዲያ ለዚህ ፋውንዴሽን የተለየ መብት የሚሰጠው ለምንድ ነው? በማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንዲህ አይነት ነገሮች ሲፈጠሩ እየታየ ይፈቀዳል ይላል። የአቶ መለስም ፋውንዴሽንም በዚያ መሰረት መስተናገድ ሲገባው እዚህ ላይ ግን ሁሉንም ነገር ማስገባት እንደሚችል መቀመጡ አግባብነት የለውም። ይህ ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ እና ልክ እንደሌሎቹ በአዋጅ 621/2001 እየተያ መሆን እንዳለበት፤ ለማነኛውም ግን ይህ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ይፋ ውይይት እንዲቀርብ ወደቋሚ ኮሚቴ ቢመራ ይሻላል የሚሉት፤ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ለነዚህ ሃሳቦች የተሰጠውን መልስ የተሰጠበትን ስሜት መግለፅ ባልችልም (የወረደ፣ የዘቀጠ፣ ወዘተን ጨምሮ) ፀረ ህዝብ የሚል መደምደሚያ የተደረሰባቸው ማብራሪያዎች ግን የሚከተሉት ናቸው (ቅኔው ሲያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት ዓይነት ነው)፡፡ በነገራችሁ ላይ ይህ ስብሰባ በዝግ መካሄዱን ያነበብኩት ከሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ነው፡፡

  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለዕረፍት ከወጣትነት እስከ ህልፈተ ህይወት ለህዝብ የሰሩ መሆናቸው፤
  • ህዝቡ አልቅሶዋል፤ ህዝቡ ለመንግስት አደራ ሰጥቶዋል፤ ይህንን አይተው አቶ ግርማም የሕዝብ ስሜት የተረዱ መስሎን ነበር፤ ነገር ግን ጉዳዩ ሌላ ነው፤
  • እንዴት መለስና ኃይለስላሴ ይወዳደራሉ
  •  የቀረጥ ነፃ መብት መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ለሚሉዋቸውም እንኳን ተሰጥቶዋል፤ ይህን ድርጅት የሚመሩት ደግሞ ሃላፊነት የሚሰማቸው ትልልቅ ሰዎች እንደሚሆኑ፤
  • ይህንን ሃሳብ ለመሰንዘር እንድትመረጥ እና እንድትናገር ያደረገህ መለስ ነው፤
እነዚህ ማብራሪያዎች በግልፅ ላስቀመጥኳቸው አሰተያየቶች መልስ አይደሉም፡፡ ፀረ-ህዝብ ያሰኙኝን ሃሳቦችን በአጭሩ ልድገማቸው፡፡

1.      የመለስ ፋውንዴሽን መቋቋም ያለበት በመለስ ደጋፊዎችና አድናቂዎች እንጂ የመለስን ፍልስፍና የማይቀበሉ ሰዎች በሚከፍሉት ግብርና ታክስ መሆን የለበትም፤ የፋውንዴሽኑ ጠቅላላ ጉባዔም መመስረት ያለበት ይህንን መሰረት አድርጎ ነው፤

2.      ፋውንዴሽኑ መቋቋም ያለበት በአዋጅ ቁጥር 621/2001 መሰረት መሆን አለበት፤

3.      የተለየ ከቀረጥ ነፃ መብት መስጠት ለምን አስፈለገ የሚሉት ናቸው፤

ውድ አንባቢያን እስኪ የቱ ገለፃና ማብራሪያ ነው ፀረ ህዝብ የሚያሰኘው፡፡ እንኳን ፀረ-ህዝብ፤ ፀረ-ኢህአዴግና ፤ ፀረ-መለስ ፋውንዴሽን የሚያሰኝ ነገር አላቀረብኩም፡፡ የማምንበትንና ማታ ትራሴ ላይ የማይጎረብጠኝን ሃሳብ በሰነዘርኩ እንደዚህ መባል ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ አሁንም ግን ግልፅ መሆን ያለበት በማስፈራሪያ የመለስን ፍልስፍና እንደማልቀበል ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ 80 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ደግፎት ቢሆንም እንኳን ብቻዬን እቆማለሁ፡፡ ነገሩ እንደዛ አይደለም እንጂ፡፡ የተከበሩ አቶ አስመላሽም ሆኖ ሌሎች ጓዶቻቸው እንዲያውቁት የሚያስፈልገው ነፃነት ማለት ታዋቂው ፀኃፊ ጆርጅ ሆርዌል እንዳለው ለህዝቡ መስማት የማይፈልገውንም ጭምር መንገር የሚያስችል መብት ነው፡፡ (“If liberty means anything at all, it means the right to tell people what they do not want to hear.”)

 የይስሙላ ዲሞክራሲ ስርዓት ባለቤትነትን አልቀበልም፡፡ በሀገራችን የ ፖለቲካ ትግልየሚለውን ቃል መለወጥ ያላስቻለን ስርዓት እንዳንቆለጳጵስ ጠብቀው ከሆነ ተሳሰተዋል፡፡ ትግል የሌለበት ፖለቲካ እስኪመሰረት ድረስ የማይወዱትንም ቢሆን መስማት ግዴታ ነው፡፡ የኢህአዴግ ታጋዮች አሁን የደረስንበት ደረጃ የመጨረሻ መስሎዋችሁ ከሆነ ትክክል አይደለም፡፡ ብዙ ቀሪ መንገድ አለን፡፡ ምርጫን ከሞትና ነውጥ ጋር ሳይሆን በአምስት ዓመት እንደሚመጣ ካርኒቫል ማየት እስክንጀምር የፖለቲካ ትግሉ ይቀጥላል፡፡
በመጨረሻም አቶ መለስ በአለም ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው በሚለው አከራካሪ ጉዳይ ለዛሬ ባለመስማማት እንስማማ፡፡ አቶ መለስ ተፅዕኖ ስለፈጠሩ በእርሳቸው ፍልስፍና መገዛት ግዴታ እንዴት እንደሚሆን ማስረዳት የሚችል ካለ ያስረዳኝ፡፡ ማርክስ፤ ሌኒን፤ አሾ፤ ወዘተ በዓለም ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በእነርሱ ፍልስፍና መገዛት ግን ግዴታ አይደለም፡፡

 የተከበሩ አቶ አስመላሽ ያልተረዱት እንዲህ ዓይነት ግዴታን የሚጥል ስርዓት የሚዘረጋ ፍልስፍናን ነው ተቀበል እያሉኝ ያሉት፡፡ አልቀበልም ያልኩት ይህንን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዓለማችን ተፅዕኖ የፈጠሩትን የነ አብራሃም ሊንከንና የነማህተመ ጋንዲን ፍልስፍና ኢህአዴጎች አልተቀበሉም፤ ተቀበሉ ብሎ የሚያስገድድም የለም፡፡ ነገር ግን የእነርሱን ፍልስፍና ነው የከሰረ የኒዎ ሊብራል ፍልስፍና እያሉ ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ መብት ነው፡፡

መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ማለት የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን መቀበል ከሆነ በግልፅ በአዋጅ ይነገረን፤ ከተሰማማን እንተገብራለን ካልተስማማን አማራጭ እንፈልጋለን፡፡

ልዩነት ለዘላለም ይኖር
-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
አቶ ግርማ ሰይፉ መድረክን ወክለው ፓርላማ ውስጥ የሚገኙ ብቸኛ ተቃዋሚ ናቸው።
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 2, 2013

No comments:

Post a Comment